የሀገር ውስጥ ዜና

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገትን በአግባቡ ማሥተዳደር ይገባል- አፈ-ጉባዔ አገኘሁ

By ዮሐንስ ደርበው

October 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም ላይ እየታየ ያለውን ፈጣን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት በአግባቡ ማሥተዳደር እንደሚያስፈልግ የፌደሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር አስገነዘቡ፡፡

አፈ-ጉባዔው በጄኔቫ እየተካሄደ በሚገኘው 149ኛው ‘ኢንተር ፓርላሜንት’ ኅብረት ጉባዔ ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም በዓለም ላይ እየታየ ያለውን ፈጣን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት በአግባቡ ማሥተዳደር እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በአዲሱ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘመን ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራን ለበለጠ ሰላማዊና ዘላቂ አኗኗር ለመጠቀም የሚስችል የአሥተዳደር ማዕቀፍ ማበጀት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ÷ ጉባዔው በጉዳዩ ላይ ትርጉም ያለው ውይይት ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ፓርላማዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማሥተዳደር ሕጋዊ ደንብ በማውጣት ረገድ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸው÷ ችግሮችን ለመፍታትና የቴክኖሎጂ መሻሻል የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ለማሳደግ በመንግሥታት መካከል የጋራ ርምጃ እንዲወሰድም ጠይቀዋል።

ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለተሻለ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለመጠቀም ሥነ-ምግባርን በተላበሰ መልኩ ለመተግበር የኅብረቱ ቻርተር አዎንታዊ ሚና ይጫወታል ማለታቸውን በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂና ብሔራዊ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፖሊሲ ማዕቀፍን ጨምሮ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለአዎንታዊ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለመጠቀም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችንም አብራርተዋል፡፡

በመንግሥት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆኖ በቂ የዲጂታል መሰረተ-ልማት ግንባታ አለመኖር እና የአቅም ክፍተት አሁንም እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውንም በዚሁ ወቅት ጠቅሰዋል፡፡

ለዚህም የዲጂታል ሽግግርን ለማቀላጠፍ የተሻለ ትብብርና አጋርነት እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዘላቂ ልማት ግቦችና አጀንዳ 2030 በመላው ዓለም እንዲሳካ ኅብረቱ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ የዘወትር ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡