የሀገር ውስጥ ዜና

ሜታ-ፌስቡክ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የደንበኞች ተሞክሮ የሚያሻሽል ፕሮግራም ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን ገለጸ

By Shambel Mihret

October 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሜታ-ፌስቡክ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የደንበኞች ተሞክሮ የሚያሻሽል ፕሮግራም በኢትዮጵያ ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ከሜታ-ፌስቡክ የመካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ የንግድ ልማት እና ስትራቴጂክ አጋርነት ዳይሬክተር ቪካስ ሜኖን እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የደንበኞችን የዲጂታል ተሞክሮ ለማሻሻል በሚረዱ ጉዳዮች ላይ ስትራቴጂያዊ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ሜታ-ፌስቡክ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የደንበኞችን ዳታ አጠቃቀም የሚያሻሽል ፕሮግራም በኢትዮጵያ ለመጀመር መወሰኑን አስታውቋል፡፡

ይህም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ያለውን ትብብር ወደላቀ ደረጃ እንደሚያያርስ መገለጹን የኢትዮ ቴሌኮም መረጃ ያመላክታል፡፡

ማዕቀፉ ደንበኞች አካውንታቸው ውስጥ ሂሳብ ባይኖርም የሜታ-ፌስቡክ አገልግሎቶችን ለተወሰነ ጊዜ በነጻ በመጠቀም ግንኙነታቸውን እንዲያስቀጥሉ ከማስቻል ባሻገር እንደ ጤና፣ ትምህርት እና የስራ እድሎች የመሳሰሉ ጠቃሚ መረጃዎችን ከክፍያ ነጻ በማቅረብ በመረጃ የበለጸገ ንቁ ዜጋ ለመፍጠር ያስችላል ተብሏል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ፍሬህይወት ታምሩ በዚሁ ወቅት÷ ሀገራዊ የይዘት ፈጠራ እንዲጎለብት ማድረግ እና የዲጂታል ስነምህዳሩን የሚያሻሽሉ ፋይዳ ያላቸው ፕሮግራሞችን መተግበር እንዲሁም የሳይበር ደህንነት እና መረጃ አያያዝን በጋራ አስተማማኝ ስለማድረግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የስምምነቱ ትግበራ የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነትን እና አካታችነትን በመጨመር የኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ሊትሬሲ በማሳደግ እንዲሁም ለደንበኞች የላቀ ተሞክሮ በማምጣት ለሀገራችን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እድገት የላቀ ሚና ይጫወታል፡፡