አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐሰተኛ እና የጥላቻ ንግግር በሀገራት ላይ የደቀኑትን አደጋ ለመከላከል የተቀናጀ ርብርብ እንደሚጠይቅ ተመላከተ፡፡
በቻይና ሺያን የ ‘ቤልት ኤንድ ሮድ’ አባል ሀገራት የልሂቃንና የመገናኛ ብዙኃን መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩም የሰው ሠራሽ አስተውሎት መስፋፋት እንዲሁም ፈጣን የቴክኖሎጂ ዕድገት ሐሰተኛ እና የጥላቻ ንግግሮች እንዲስፋፉ በር መክፈቱ ተነስቷል።
ይህም በተለያዩ ሀገራት ግጭቶች እንዲስፋፉ ከማድረግ ባሻገር ለሀገራት የተዛባ ምስል እስከመስጠት የደረሱ ጉዳቶች እያስከተለ መሆኑን በመድረኩ ላይ የቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች ውጤቶች አመላክተዋል፡፡
እነዚህን ወሰን አልባ ችግሮች ለመከላከል የተለያዩ ሀገራት በቅንጅት የተደራጁ ሥራዎችን ለማከናወን ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው በአጽንኦት ተገልጿል፡፡
የሀገራት መገናኛ ብዙኃንም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ለመፍትሔው በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ነው የተገለጸው፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቻይና መገናኛ ብዙኃን ከተለያዩ ሀገራት መገናኛ ብዙኃን ጋር በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ