ዓለምአቀፋዊ ዜና

ኔታንያሁ በሂዝቦላህ ድሮን ጥቃት የተጎዱ የእስራኤል ወታደሮችን ጎበኙ

By Melaku Gedif

October 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሂዝቦላህ ድሮን ጥቃት የተጎዱ የሀገሪቱ ወታደሮችን በሳህባ የሕክምና ማዕከል ጎብኝተዋል፡፡

ኔታንያሁ በዚህ ወቅት÷”በእስራኤል የነጻነት ቀን የቆሰሉ ጀግኖችን መጎብኘትና የሥነ-ልቦና ጥንካሬያቸውን መስማት ለኔ ልዩ እድል ነው” ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው መታደሮች በፍጥነት እንዲያገግሙም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

ትናንት ምሽት ሂዝቦላህ በእስራኤል ደቡባዊ ሃይፋ ቤኒያሚና ወታደራዊ ካምፕ ጎላኒ ብርጌድ ላይ በፈጸመው ጥቃት 4 ወታደሮች ሲሞቱ ከ58 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ሕይወታቸው ያለፉት ወታደሮች በውጊያ ስልጠና ላይ የነበሩ ሲሆን÷የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸውም ነገ ጠዋታ በወታደራዊ ትርዒት ታጅቦ ይፈጸማል ተብሏል፡፡

እስራኤል በሂዝበላህ ላይ እርምጃ መውሰድ ከጀመረች ጊዜ አንስቶ ከባድ የተባለው ጥቃቱ÷የእስራኤልን የአየር መቃወሚያ እንዴት አለፈ የሚለው እያነጋገረ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

ሂዝቦላህ በበኩሉ የድሮን ጥቃቱን መፈጸሙንና ለጥቃቱ ሃላፊነት እንደሚወስድ ገልጾ፤ሊባኖስን እንከላከላለን ሲል ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘግቧል፡፡