የሀገር ውስጥ ዜና

 ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 548 ነጥብ 66 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሄራዊ ባንክ ገባ

By Mikias Ayele

October 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2017 ዓ.ም በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 548 ነጥብ 66 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሄራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን የክልሉ ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሃላፊ አቶ አድማሱ ሞርካ÷በክልሉ ባለፉት ጊዜያት በማዕድን ዘርፍ በነበሩ የተለያዩ ተግዳሮቶች በሚጠበቀው ልክ አለመሰራቱን ተናግረዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት 40 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሄራዊ ባንክ ገቢ ለማድረግ ታቅዶ 548 ነጥብ 66 ኪሎ ግራም ገቢ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

በቅርቡ የተደረገውን ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ የተሻሻሉ አሰራሮች ለተመዘገበው ውጤት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል በሩብ ዓመቱ 15 ሺህ ቶን የድንጋይ ከሰል እንዲመረት እቅድ ተይዞ 27 ሺህ 573 ቶን የድንጋይ ከሰል መመረቱን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም 600 ሜትር ኪዩብ እምነበረድ ለማምረት ታቅዶ 459 ነጥብ 4 ሜትር ኪዩብ ማምረት እንደተቻለ መግለጻቸውንም የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡፡