ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ ወታደሮችን በመላክ ድጋፍ እያደረገች ነው ስትል ዩክሬን ከሰሰች

By ዮሐንስ ደርበው

October 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ ወታደሮችን በመላክ በጦርነቱ እየተሳተፈች ነው ሲሉ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ከሰሱ፡፡

ሰሜን ኮሪያ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ ለምትገኘው ሩሲያ ወታደሮቿን በመላክ ጭምር እገዛ እያደረገች ስለመሆኗ ተናግረዋል።

ተጨማሪ ድጋፎችን አጋር ሀገራት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለመጠየቅ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፤ ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ በሰው ሃይል ጭምር ድጋፍ እየተደረገላት እንደሆነ በመግለጽ ወንጅለዋል።

ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ለአጋር ምዕራባዊያን አጋሮቻቸው የጦር መሳሪያ እና የሰው ሃይልን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ ተከታታይ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።

የሩሲያ ጦር ከርስክ አካባቢን ለመቆጣጠር እየሞከረ ቢሆንም የዩክሬን ሰራዊት የሩሲያን ግስጋሴ እየገታ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ መናገራቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡