Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የእንጨት ዕደ-ጥበብ ባለሙያው ወጣት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ነዋሪነቱን በጅማ ከተማ ያደረገው ወጣት ላይኔ ለማ እንጨት ፈልፍሎ የተለያዩ የዕደ-ጥበብ ውጤቶችን በመስራት በበርካቶች ዘንድ በስራዎቹ አድናቆትን አትርፏል።

በእንጨት ቅርጻቅርጽ ጥበብ ሙያ እንዲሰማራ ወላጅ አባቱ በጎ ተጽህኖ እንዳሳረፉበት የሚናገረው ላይኔ ስራውን ከጀመረ አምስት አመት እንደተቆጠሩ ይገልጻል።

ጅማ በእንጨት ጥበብ ውጤቶች የምትታወቅ ቢሆንም ሙያውን በማሳደግ ረገድ እምብዛም የተሰሩ ስራዎች አለመኖራቸው ቁጭት አሳድሮበት ወጥ ከሆነ እንጨት የሚፈለፈሉ የተለያዩ የዕደ-ጥበብ ስራዎችን መስራት እንደጀመረ ተናግሯል።

ወጣቱ የሚሰራቸውን ልዩ ልዩ የእንጨት ዕደ-ጥበብ ስራዎች በእጅ ስልኩ እየቀረጸም በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት በማስተዋወቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ በጎ ምላሽ እንዳገኘ ገልጿል።

ወጣቱ በቤቱ የሚገለገልባቸውን ቁሳቁሶች በሙሉ የእንጨት ውጤቶች በማድረግ ከእንጨት ጋር ያለውን ፍቅር እንደሚገጽ ተናግሯል።

እሱን ጨምሮ በከተማው በእንጨት ስራ ጥበብ የተሰማሩ የተለያዩ ወጣቶች ሙያው ውስጥ እንዲቆዩ የሚያደርጋቸው ለስራው ያላቸው ፍቅር እንጂ የሚገኘው ገቢ አመርቂ እንዳልሆነ ገልጿል።

 

የእንጨት እደ ጥበብ መማሪያ ት/ቤት መክፈት የወደፊት ህልሙ እንደሆነ የሚገልጸው ወጣት ላይኔ አሁን ተከራይቶ ከሚሰራበት ቦታ ወጥቶ ስራውን አስፋፍቶ እንዲሰራ ያለበት የመስሪያ ቦታ ችግር እንዲቀረፍለትም ጠይቋል።

በወርቃፈራሁ ያለው

Exit mobile version