የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደህንነትን አደጋ ላይ ለመጣል በመንቀሳቀስ የተከሰሱ ግለሰቦች የክስ መቃወሚያ አቀረቡ

By Feven Bishaw

October 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል በመንቀሳቀስ የተከሰሱ ስድስት ግለሰቦች ክሱ እንዲሻሻል የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ አቀረቡ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የቀረበውን የክስ መቃወሚያ መርምሮ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በዛሬው ቀጠሮ የክስ መቃወሚያቸውን በጠበቆቻቸው አማካኝነት ያቀረቡት ተከሳሾቹ ዮሃንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል)፣ አማኑኤል መውጫ፣ ናትናኤል ወንድወሰን፣ ኤልያስ ድሪባ፣ ይዲድያ ነጻነት እና እሌኒ ክንፈ ናቸው።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ በነ ዮሃንስ ዳንኤል መዝገብ በስድስት ተከሳሾች ላይ አውሮፕላንን ያለአግባብ መያዝ ወንጀል፣ የመንግስት ሰራተኛ የስራ ግዴታውን እንዳይፈጽም መቃወምና አለመታዘዝ ወንጀል ክስ በተጨማሪም በ1ኛ ተከሳሽ ብቻ ደግሞ የአየር መንገዱን መልካም ስም ለሚያጎድፍ በተንቀሳቃሽ ምስል በኮምፒዩተር ስርዓት አማካኝነት ማሰራጨት ወንጀል የሚል ክስ ማቅረቡ ይታወሳል።

ተከሳሾቹ የክሱ ዝርዝር ከደረሳቸው በኋላ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ በተሰጠ ትዕዛዝ መሰረት ዛሬ ከማረሚያ ቤት ቀርበው ጉዳያቸውን ተከታትለዋል።

በዚህም የተከሳሽ ጠበቆች የክስ ዝርዝሩ እንዲሻሻል የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ በጽሁፍ አቅርበዋል።

ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች በኩል በቀረበው የክስ መቃወሚያን በሚመለከት ዐቃቤ ሕግ ከቀጠሮ በፊት መልሱን (አስተያየቱን) በሬጅስትራር በኩል እንዲያቀርብ በማለት በአጠቃላይ በመቃወሚያው ላይ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀጥሯል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ተከሳሾቹ ከዚህ ቀደም በስር ፍርድ ቤት የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ጠይቀው በሂደት ላይ ይገኛል።

በታሪክ አዱኛ