የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ እንዳሻው ጣሰው ኢትዮጵያን መጠበቅ የዘመኑ ትውልድ ኃላፊነት መሆኑን አስገነዘቡ

By amele Demisew

October 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋራ አስተሳስራ ያኖረችንን ሀገር መጠበቅ የዚህ ዘመን ትውልድ ትልቅ ኃላፊነት ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰው አስገነዘቡ፡፡

በክልሉ 17ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡

ርዕሰ መሥተደድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ሀገራችን ባሳለፈቻቸው ረጅም ዓመታት ዳር ድንበሯን ጠብቃ፣ ከውጭ የመጡ ጠላቶችን መክታና ሉዓላዊነቷን አስከብራ ኖራለች።

ጀግኖች አባቶቻችን ሉዓላዊነቷን ያስጠበቁልንን ሀገር የዚህ ዘመን ትውልድ በልማት ስራ ላይ በማተኮር ውጤት ለማስመዝገብ መትጋት እንደሚጠበቅበት መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

ሰንደቅ ዓላማችን ኢትዮጵያ ነች ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ÷ በጋራ ያስተሳሰረችንን ሀገር መጠበቅ የዚህ ዘመን ትውልድ ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡