አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ከፍ በማድረግ እና አንድነታችንን በማጽናት ሊሆን እንደሚገባ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አስገነዘቡ፡፡
በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ከተማ 17ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ መርሐ ግብሮች ተከብሯል፡፡
ቀኑ “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ የተለያዩ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ መልዕክቶች በማስተላለፍ ነው የተከበረው፡፡
ርዕሰ መስተዳደሩ ደስታ ሌዳሞ በዚህ ወቅት÷ ” ሰንደቅ ዓላማ ለአንድ ሀገር ሉዓላዊነት መገለጫ በመሆኑ ቀኑን ስናከብር ሉዓላዊነታችንን ለማፅናትና የሰንደቅ ዓላማችንን ክብር ከፍ ለማድረግ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
የሰንደቅ ዓላማችንን ክብር በመጠበቅ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ለሚደረገው ርብርብ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡