አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ወደ ተፈፃሚነት መግባት ቀድሞ የነበሩ አሳሪ ሕጎችን በመሻር ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር ኢ/ር ) ገለጹ።
የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ወደ ተፈፃሚነት መግባቱን ተከትሎ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር ) ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
የትብብር ማዕቀፉ 45 አንቀፆች እንዳሉት ያነሱት ሚኒስትሩ÷ የጋራ ተጠቃሚነት እና መረጃ መለዋወጥን ጨምሮ የተለያዩ መርሆችን የያዘ ነው ብለዋል።
ትናንት ወደ ተፈፃሚነት የገባው የትብብር ማዕቀፍ ከዚህ ቀደም የነበሩ ለአንድ ወገን ያደሉ አሳሪ ሕጎችን በመሻር ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑንም አንስተዋል።
ማዕቀፉ ማንንም የመጉዳት ዓላማ እንደሌለው አፅዕኖት የሰጡት ሚኒስትሩ፤ በትብብር መልማትን እና በጋራ መጠቀምን ግብ ያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የማዕቀፉ ወደ ተፈፃሚነት መግባት ኢትዮጵያ ትልቅ ድል የተቀዳጀችበት በመሆኑ ሚና የነበራቸው አካላትና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊመሰገኑ ይገባልም ብለዋል፡፡
በወንድሙ አዱኛ