የሀገር ውስጥ ዜና

ኮሚሽኑ ነገ በሶማሌ ክልል የምክክር መድረክ ይጀምራል

By Feven Bishaw

October 13, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስተባባሪነት በሶማሌ ክልል የሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ነገ ይጀምራል፡፡

በክልሉ ከነገ ጀምሮ የሚካሄደውን የምክክር መድረክ በተመለከተ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው÷ ኮሚሽኑ እስካሁን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ፣ በሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በአፋር ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኮችን አካሂዶ አጀንዳዎችን መረኩቡን አስታውሰዋል፡፡

በሶማሌ ክልል ደግሞ ከነገ ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ እንደሚካሄድ የጠቆሙት ኮሚሽነር መላኩ በክልሉ ከሚገኙ 95 ወረዳዎች፣ ከ6 የከተማ አስተዳደሮች እና ከ4 የጅግጅጋ ክ/ከተሞች የተወከሉ ተሳታፊዎች በምክክሩ እንደሚሳተፉ አብራርተዋል፡፡

እንደ ኮሚሽር መላኩ ማብራሪያ የሶማሌ ክልል የምክክር መድረክ በሁለት ምዕራፍ የሚካሄድ ይሆናል፡፡

በመጀመሪያው ምዕራፍ ከነገ እስከ መጪው ረቡዕ ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም በክልሉ 10 የማህበረሰብ መሰረቶችን የወከሉ ከ2ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በሶስት ማዕከላት ማለትም በጅግጅጋ፣ በጎዴና በዶሎ አዶ ማዕከላት ተከፋፍለው ከወከሉት ማህበረሰብ ይዘዋቸው በመጡ አጀንዳዎች ላይ የሚመካከሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በጅግጅጋ በሚካሄደው የምክክር መድረክ ከ1ሺህ በላይ፣ በጎዴ ከ650 በላይ እንዲሁም በዶሎ አዶ ማዕከል ከ350 በላይ የማህበረሰብ ወኪሎች እንደሚሳተፉም ገልጸዋል፡፡

የማህበረሰብ ወኪሎች ምክክር ከተጠናቀቀ በኋላ ከሶስቱ ማዕከላት የተመረጡ 100 የህብረተሰብ ወኪሎችን ጨምሮ አምስቱ የክልሉ የምክክር ባለድርሻ አካላት ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ጅግጅጋ ከተማ ተገናኝተው በክልሉ አጀንዳዎች ላይ ለተከታታይ ሶስት ቀናት የሚመካከሩ ይሆናል፡፡

በዚህ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ የህብረተሰብ ወኪሎችን ጨምሮ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከመንግስት አስፈፃሚ አካላት፣ ከልዩ ልዩ ተቋማትና ማህበራት እንዲሁም ከተፅኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የተወከሉ ከ1ሺህ በላይ ተወካዮች የሚሳተፉ ይሆናል፡፡

ይህ መርሃ ግብር ወሳኝ ምዕራፍ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በምክክሩ በንቃት እንዲሳተፉ ኮሚሽር መላኩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

በቅድስት አባተ