የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ በመልሶ ማልማት ለተነሱ ዜጎች አገልግሎት የሚውል ት/ቤት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

By amele Demisew

October 13, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመልሶ ማልማት ለተነሱ ዜጎች አገልግሎት የሚውል ከቅድመ አንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል።

የትምህርት ቤቱ ግንባታው በሁለት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን የተመላከተ ሲሆን÷በተጨማሪም በአካባቢው የትራንስፖርት እና የመንገድ ሥራ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተጠቁሟል።

እንዲሁም ከንቲባ አዳነች በመልሶ ማልማት ከካዛንችስ እና አካባቢው የተነሱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ገላን ጉራ በመገኘት ቤት ለእምቦሳ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።

የካዛንቺስ ነዋሪዎች ትልቅ አርዓያነት ያላቸው የአዲስ አበባ ባለውለታዎች መሆናቸውን የገለጹት ከንቲባዋ ፤ሀገርን የሚጠቅመው እንደዚህ ተነጋግሮ መግባባት ነው ብለዋል።

ሁልጊዜ የሰው ሀገር አድናቂ መሆን የለብንም ያሉት ከንቲባዋ፤ ሕዝብ ለተጋራው ራዕይ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንስራ ሲሉም መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመርኃ-ግብሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ እና ለአካባቢው ነዋሪዎች ማዕድ አጋርተዋል።