የሀገር ውስጥ ዜና

ከተማ አስተዳደሩ ከፌደራል ፖሊስ ጎን ሆኖ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ያደርጋል-ከንቲባ አዳነች

By Feven Bishaw

October 13, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚችለው ሁሉ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጎን ሆኖ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ያደርጋል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና በአስተዳደሩ ከከፍተኛ እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የለውጥ ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

በዚህ ወቅት ከንቲባ አዳነች÷ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር በቅንጅት በተሠራው የፀጥታ ሥራ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም በዘላቂነት ተጠብቆ ሕዝቧ በተረጋጋ ሁኔታ የዕለት ተዕለት ኑሮውን መምራት አስችሏል ብለዋል፡፡

ከንቲባዋ አያይዘው የፌደራል ፖሊስ ለውጡን በትጋት እያሳለጠ እንደሚገኝ በጉብኝታቸው መገንዘባቸውን እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በሚችለው ሁሉ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጎን ሆኖ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል÷ተቋሙ ባከናወናቸው የለውጥ ሥራዎች አሁን ላይ የሕዝብ አመኔታ እያገኘ መምጣቱን መግለፃቸውን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፀጥታ እና ደህንነት አካላት እንዲሁም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በትብብር በመሥራቱ ከተማዋ ከሽብር ስጋት እና ጥቃት ነጻ ሆና ዜጎች በሰላም የሚንቀሳቀሱባት እንደሆነች ኮሚሽነር ጀነራል ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሚሰጠው ፖሊሳዊ አገልግሎት እና በታጠቃቸው ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ በመሆን ከሌሎች ዓለም ሀገራትም ዕውቅና እያገኘ መምጣቱንም ገልጸዋል።

ከንቲባዋ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትንም የጎበኙ ሲሆን በዚህ ወቅት ÷አሰራርን የሚያዘምኑና ቅልጥፍናን የሚጨምሩ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂዎችን በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን መሰራቱ የሚያኮራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡