አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተባበርን እና ከተደጋገፍን ሁላችንም በጋራ በመልማት ጠንካራ ቀጣና መፍጠር እንችላለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ፡፡
የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ከዛሬ ጀምሮ ወደ ተፈጻሚነት ገብቷል፡፡
ይህን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ በናይል ወንዝ ተፋሰስ ላይ የተደረገው የማዕቀፍ ስምምነት ወደ ተፈጻሚነት መግባት ለጋራ ብልጽግናችን የጀርባ አጥንት ነው ብለዋል፡፡
በናይል ወንዝ ተፋሰስ ላይ የተደረገው የማዕቀፍ ስምምነት (ሲ ኤፍ ኤ) ወደ ተፈጻሚነት መግባት የአባይ ወንዝ ውኃን በፍትሐዊነትና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የተሄደበትን ረጅም ጉዞ የቋጨ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱ ወደ ተፈጻሚነት የገባበት የዛሬው ቀንም ለተፋሰሱ ሀገራት ታሪካዊ መሆኑን ገልጸው÷ እውነተኛ ትብብርን ለማጎልበት በጋራ ለምናደርገው ጥረት መሰረት ነው ብለዋል፡፡
የማዕቀፍ ስምምነትቱ ወደ ተፈጻሚነት መግባቱ እንደ ናይል ወንዝ ተጠቃሚ ሀገራት ያለንን ትስስር ያጠናክርልናል ሲሉም አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም የጋራ ሃብታችን የሆነው የናይል ወንዝ ለሁላችንም ጥቅም እንዲውል ያስቻለ ነው ብለዋል።
ይህ የማዕቀፍ ስምምነት እውን እንዲሆን ላስቻሉ አካላትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል ስምምነቱን ያልፈረሙ አካላት እንዲፈርሙ ጥሪ አቅርበው÷ ከተባበርን እና ከተደጋገፍን ሁላችንም በጋራ በመልማት ጠንካራ ቀጣና መፍጠር እንችላለን ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡