Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ወደ ተፈጻሚነት ገባ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ከዛሬ ጀምሮ ወደ ተፈጻሚነት መግባቱን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሐብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሩ ስምምነቱ ወደ ተፈጻሚነት መግባቱን አስመልክተው የናይል የትበብር ማዕቀፍ ስምምነት ተፈጻሚነት ማብሰሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም÷ የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ከዛሬ ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ  ወደ ተፈጻሚነት መግባቱን አስታውቀዋል፡፡

ይህን ተከትሎም የዛሬው ቀን በናይል ተፋሰስ ታሪክ ልዩ መሆኑን አንስተው÷ መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ የተፋሰሱ ሀገራት መንግሥታትና ሕዝቦች ለዚህ ታሪካዊ ስኬት በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

ለዚህ ስምምነት ከጥንስሱ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በተለያየ መንገድ አስተዋጽዖ ላበረከቱ  ኢትዮጵያውያንም ሚኒስትሩ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

የናይል የትብብር ስምምነት ተፈጻሚ መሆን የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽንን መመስረት እንደሚስችል ጠቅሰው÷ ኮሚሽኑ ለሁሉም ተጠቃሚነት የናይል ወንዝን የማስተዳደርና የመጠበቅ ኃላፊነት ይወስዳል፤  የትብብሩም የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ያገለግላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ የሕግ ማዕቀፍ፣ የናይልን ወንዝ ለሁላችንም ጥቅም ለማዋል የጋራ ቁርጠኝነታችን ምስክር እንዲሁም የውኃ ሀብቱን በእኩልነትና ፍትሐዊነት የመጠቀም መብት ማረጋገጫ የሚሆን ስምምነት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የናይል የውኃ አጠቃቀምን በተመለከተ የነበረውን  ኢ-ፍትሐዊነት ያስተካክላል፤ የሁሉንም የናይል ሀገሮች የጋራ ሀብት ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል ብለዋል በመግለጫቸው፡፡

በተጨማሪም ስምምነቱ ለሁሉም የናይል ተፋሰስ ሀገሮች ሕጋዊ መብት ዕውቅና እንደሚሰጥ ገልጸው÷ ሁላችንንም ለውኃው ፍትሐዊ ክፍፍልና ለዘላቂ አጠቃቀም ተገዥ ያደርገናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

እያንዳንዱ ሀገር የሌላውን መብት ሳይጋፋ በጋራ የሚያድግበትና የሚበለጽግበት የሁሉንም መጻኢ ተስፋ እንደሚወክልም አመላክተዋል፡፡

ዘላቂ ልማት የትብብር ስምምነቱ ማዕከል ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ የናይልን የውኃ ሀብት ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ከእኛ በኋላ ለሚመጡት ትውልዶችም እንዲሆን አድርገን መጠቀም የሚያስችል ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ስምምነቱ ናይልንና ከባቢውን እንድንጠብቀው፣ ውኃውን የወደፊቱን ተጠቃሚ በማይጎዳ መልኩ እንድንጠቀም ያስገድደናል ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

ሁሉም የተፋሰሱ ሀገሮች ስምምነቱን  እንዲቀላቀሉትና መርሆዎቹን በታማኝነት እንዲፈጽሙ ጥሪ ያቀረቡት ሚኒስትሩ÷ የናይል ወንዝ የተስፋ ምንጭ የሚሆንበትን፣ ተግዳሮቶችን በጋራ የምናቃልልበትና ለራሳችንና ለመጪው ትውልድ የተሻለ  ዓለም የምንፈጥርበትን መጻኢ ጊዜ ለመገንባት በጋራ እንሥራ ብለዋል፡፡

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም በትብብር ጉዟቸው ላደረጉት አስተዋጽኦ አመሥግነው÷ ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ በምናደርገው ጉዞም አጋርነታቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

Exit mobile version