የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል 110 ሺህ ሄክታር የደረሰ ሰብል ተሰበሰበ

By Shambel Mihret

October 12, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በመኽር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከለማ መሬት በ110 ሺህ ሄክታር ላይ ቀድሞ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ በክልሉ በመኽር ወቅት 5 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለምቷል።

ቀድሞ የደረሰን ሰብል ለመሰብሰብ በተደረገ እንቅስቃሴ በ110 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ገብስ፣ ጤፍ፣ ሰሊጥ፣ ቦሎቄ እና ሌሎች ሰብሎች ለመሰብሰብ መቻሉን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች እየጣለ ያለው ከመደበኛው ያልተናነሰ ዝናብ የደረሱ ሰብሎችን እንዳያበላሽ አርሶ አደሩ በደቦና የቤተሰቡን ጉልበት አስተባብሮ የደረሰ ሰብሉን መሰብሰብ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ሰብሉ በዝናብ እንዳይበላሽ በአግባቡ አናፍሶና አድርቆ በመከመር ምርቱን ከብልሽት መታደግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የሚጥለው ዝናብ በቀሪ እርጥበት ለሚዘሩ ሰብሎች ጠቀሜታ እንዳለው በመግለጽ አርሶ አደሩ ሰብል ከመሰብሰብ ጎን ለጎን ፈጥነው የሚደርሱ የሰብል አይነቶችን መዝራት እንዳለበት ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡