የሀገር ውስጥ ዜና

መከላከያ በቄለም ወለጋ ዞን የወርቅ ማዕድን ሲመዘብሩ ነበሩ ያላቸውን 135 የሸኔ ሽብር ቡድን ተላላኪዎችን ያዘ

By Shambel Mihret

October 12, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር መከላከያ ሰራዊት በቄለም ወለጋ ዞን የወርቅ ማዕድን ሲመዘብሩ ነበሩ ያላቸውን 135 የሸኔ ሽብር ቡድን ተላላኪዎችን መያዙን አስታወቀ።

የማዕከላዊ ዕዝ ክፍለ ጦር ባደረገው ስምሪት በህገ ወጥ መልኩ የሀገሪቱን ሀብት ሲመዘብሩ የነበሩ የሸኔ ሽብር ቡድን ሴሎችን በቁጥጥር ማዋሉን የክፍለ ጦሩ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ሌተናል ኮሎኔል መሀመድ ኢብራሂም ገልፀዋል።

ሠራዊቱ በደረሰው ጥቆማ በቄለም ወለጋ ዞን በሀዋ ገላን ወረዳ የወርቅ ማዕድን የሚገኝበት ልዩ ስሙ ለገወርቄ በተባለ ቦታ በተደረገ የተጠናከረ አሰሳ እና ፍተሻ 135 የሽብር ቡድኑ ተላላኪዎች ተይዘዋል ብለዋል።

ተላላኪዎቹ በህገ ወጥ መንገድ ከሚያወጡት የወርቅ ማዕድን ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነውን ለሸኔ የሽብር ቡድን ይገብሩ እንደነበር ተረጋግጧል ሲሉ ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑን የግንኙነት መረብ ለመበጣጠስ በተደረገው ዘመቻ የሎጂስቲክስ እና የመረጃ ምንጭ ሆነው ሲያገለግሉ እንደነበር በአህያ ተጭኖ ሲጓጓዝ የተያዘ የፊኖ ዱቄት እና ዘይት ማረጋገጫች ነው ብለዋል።

ክፍለጦሩ በህገወጥ ተግባር የተሠማሩ እና ለቡድኑ መረጃ እና ሎጅስቲክስ የሚያደርሱትን በመከታተል ለህግ የማቅረቡን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።