የሀገር ውስጥ ዜና

 ኢትዮጵያና ርዋንዳ የሴቶችን አቅም ማጎልበት ላይ በትብብር እንደሚሰሩ ገለጹ

By Mikias Ayele

October 12, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የርዋንዳ አምባሳደር ቻርለስ ካራምባ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ኢትዮጵያና ርዋንዳ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመጋራት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት በትብብር መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)÷ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ትስስር በማሳደግ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት በትብብር መስራት እንደሚገባቸው ጠቅሰዋል።

ሩዋንዳ በጾታ እኩልነትና የሴቶችን አቅም በማጎልበት የሰራችው ሥራ የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው÷እነዚህን ተሞክሮዎች ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

አምባሳደር ቻርለስ በበኩላቸው÷ርዋንዳ የሥርዓተ-ጾታ እኩልነትንና የሴቶችን አቅም በማጎልበት በተለይም በፖለቲካ ተሳትፎ ላይ የምታደርገው ጥረት ከፍተኛ እንደሆነ መጥቀሳቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ለዚህ ማሳያም ሁለት ሶስተኛው የፓርላማ መቀመጫ እና 52 በመቶ የካቢኔ ቦታዎች በሴቶች የተያዙ መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡

በእነዚህ እና ሌሎች ሥራዎች ላይ ከኢትዮጵያጋር በትብብር ለመስራት ከዚህ በፊት ከተደረሱ ስምምነቶች ባሻገር አዲስ የስምምነት ሰነዶችን ከማዘጋጀት ጀምሮ የተለያዩ ዝግጁነቶች መኖራቸውን ገልፀዋል።