የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ የቻይና ባለሃብቶች 8 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ስራ ላይ ማዋላቸው ተገለጸ

By Feven Bishaw

October 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ የቻይና ባለሃብቶች 8 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር መዋለ ንዋይ ስራ ላይ በማዋል ለሀገር ዕድገት ገንቢ ሚና እየተጫዎቱ መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎችና የመገናኛ ብዙኃን ሙያተኞች በዱከም የኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን የሊንዳ ኢትዮጵያ ጋርመንት፣ ሁዋጃ አሉሙኒየምና ዲ ዋን ሴራሚክስ የተሰኙ የቻይና ኩባንያዎችን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ በፌደራልና በክልል መንግስት እንዲሁም በቻይና ባለሃብቶች ለተገነቡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መሰረተ ልማት ማሟላት ተችሏል።

ጉብኝት የተደረገበት የኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክም 153 የውጭ ባለሃብቶች የሚያለሙበትን ዕድል በመፍጠር በኢትየጵያ ካሉ ተቀዳሚው ግዙፍ የግል ኢንዱስትሪ ፓርክ መካከል መሆኑን አብራርተዋል።

በፓርኩ 93 ከመቶ የሚሆነውን ድርሻ የቻይና አልሚ ባለሃብቶች በተለያዩ መስኮች እያለሙ የሚገኙ ሲሆን ቀሪውን ደግሞ የህንድና የእንግሊዝ አልሚዎች መሸፈናቸውን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ከ3 ሺህ 300 በላይ የሚሆኑ የቻይና ፕሮጀክቶች በ8 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር መዋለ ንዋይ ፈሰስ በማድረግ የአንበሳውን ድርሻ ይዘዋል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የቻይና ኩባንያዎችም በተኪ ምርት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በንግድ ትስስር በሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከ325 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻሉ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኮምቤ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ ሆነው የቆዩ የገቢና ወጪ ምርት የንግድ ዘርፎች ክፍት በመደረጋቸውም የውጭ ባለሃብቶች የተሳትፎ ፍላጎት ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን አብራርተዋል።

በተለይም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተዘግተው የነበሩ የገበያ አማራጮችን ክፍት በማድረግ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ድጋፍ በማድረግ ገንቢ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

በኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን የተሰማሩ የቻይና ባለሃብቶችም በሚደርግላቸው ድጋፍ በርካታ የስራ ዕድል በመፍጠር በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።