የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ መሻሻል ያሳየ ነው – ቶኒ ብሌር

By Feven Bishaw

October 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ መሻሻል ያሳየ መሆኑን የቀድሞ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር እና የቶኒ ብሌር ኢንስቲትዩት ዋና ሊቀ መንበር ቶኒ ብሌር ተናገሩ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የቶኒ ብሌር ኢንስትቲዩት ለኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ትግበራና ስኬት የሚያደርገው አስተዋጽኦ ላይ ያተኮረ ውይይት ከቶኒ ብሌር ጋር አድርገዋል፡፡

በውይይቱ የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ካውንስል አባል የሆኑት የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) እና የዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ሃላፊ ዮዳሄ አርአያስላሴ ተገኝተዋል።

የቶኒ ብሌር ኢንስትቲዩት በዘርፉ በኢትዮጵያ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ሃላፊዎቹ፤ በቀጣይም አብሮ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ቶኒ ብሌር በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ መሻሻል ያሳየ መሆኑን ገልጸው ተቋማቸው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ካውንስሉን እንቅስቃሴ እንደሚደግፍ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ልማት፣ በዳታ አስተዳደር፣ በዲጂታል መታወቂያ እና በመሠረተ ልማት ግንባታ ዘርፎች ከየተቋማቱና ከካውንስሉ ጋር ተባብሮ እንደሚሠራና እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።