አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሂሮሺማ እና ናጋሳኪ የኒውክለር ቦምብ ጥቃት የተረፉ ጃፓናውያን ያቋቋሙት ‘ኒሆን ሂዳንክዮ’ የተሰኘው ማህበር የ2024 የሰላም የኖቤል ሽልማትን አሸንፏል።
ኒሆን ወይም ሂባኩሻ በመባል የሚታወቀው ማህበሩ ኒውክለር ቦምብ ዳግም ጥቅም ላይ እንዳይውል እየሰራ የሚገኝ ማህበር ነው።
የኖቤል ኮሚቴው ሽልማቱን ይፋ ባደረገበት ወቅት ማህበሩ ከኒውክለር መሳሪያ የጸዳች ዓለምን ለመፍጠር ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ ኒውክለር ቦምብ ዳግም ጥቅም ላይ መዋል እንደሌለበት የተግባር ምስክርነት እየሰጠ መሆኑ ተነግሯል።
የኖቤል ኮሚቴው በሰላም የኖቤል ሽልማት ዘርፍ 197 ግለሰቦችና 89 ተቋማት በአጠቃላይ 286 እጩዎች መቅረባቸውን ገልጿል።
የኮሚቴው ሰብሳቢ ጆርገን ፍራይድነስ ኒሆን ሂዳንክዮ ሽልማቱን ማሸነፉ የኒውክለር መሳሪያ ጥቅም ላይ እንዳይውል ማድረግ ተገቢ መሆኑን እንደሚያስገነዝብ ተናግረዋል።
አክለውም በጃፓን የኒውክለር ቦምብ ጥቃት አካላቸውን ላጡ እና መጥፎ ትውስታ ላላቸው ክብር እንደሚገባቸው ጠቅሰው፤ ክስተቱን ሰላማዊ ዓለም ለመፍጠር መጠቀም ይገባናል ብለዋል፡፡
የማህበሩ መሪ ቶሺዩኪ ሚማኪ ሽልማቱ የኒውክለር ጦር መሳሪያ እንዲታገድ ትግል ለሚያደርገው ማህበር ዓላማውን እውን ለማድረግ አቅም እንደሚሆነው ተናግረዋል።
የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሸጌሩ ኢሺባ ማህበሩ እስካሁን የኒውክለር የጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ እንዳይውል ረጅም ጊዜ ለሰራው ስራ የተበረከተለት የኖቤል ሽልማት ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው ማለታቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡