ቢዝነስ

ከጥራጥሬ በተጨማሪ የወጪ ንግድ ምርቶችን በስፋት ወደ አዘርባጃን ለመላክ እየተሠራ ነው

By ዮሐንስ ደርበው

October 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከጥራጥሬ ሰብል ምርቶች በተጨማሪ ሌሎች የወጪ ንግድ ምርቶችን በስፋት ወደ አዘርባጃን ለመላክ እየሠራች መሆኗን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ በኢትዮጵያ የአዘርባይጃን አምባሳደር ሩስላን ናስቦቭ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም በሁለቱ ሀገሮች መካከል የተጀመረውን የንግድ፣ ኢንቨስትመንት ትብብርና ግንኙነት በይበልጥ ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ምርቶችን በዓይነት፣ በመጠንና በጥራት በማሳደግ መዳረሻ ሀገሮችን በማስፋፋት የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንደምትሠራ ማስረዳታቸውን ጠቁመዋል።

አዘርባጃን የጥራጥሬ ሰብል ምርቶችን ከኢትዮጵያ የምታስገባ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ያላትን የወጪ ንግድ አማራጮችን አሟጥጣ በመጠቀም ሌሎች ምርቶችንም ለመላክ ያላትን ፍላጎትም አስረድተዋል፡፡

አምባሳደሩ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ በጋራ ለመስራት ያቀረቡትን ሐሳብ በመቀበል÷ በቅርቡ ከአዘርባጃን ከሚመጣው ልዑክ ጋር ለመወያየትና ቀጣይ ሥራዎችን ለመሥራት ከስምምነት ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡