የሀገር ውስጥ ዜና

ለ300 ጤና ተቋማት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ያለመ ፕሮጄክት ይፋ ሆነ

By ዮሐንስ ደርበው

October 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ300 ጤና ተቋማት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ 6 ነጥብ 7 ሚሊየን ወገኖችን የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ፕሮጄክት ይፋ ሆነ።

መርሐ-ግብሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ጨምሮ በዑጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ፓኪስታን የሚተገበር ሲሆን ለዚህ ማስፈፀሚያም 35 ሚሊየን ዶላር መመደቡ ተገልጿል፡፡

ጤና ሚኒስቴር እና የተለያዩ አጋር አካላትም ዛሬ ፕሮጄክቱን ይፋ አድርገዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም ፕሮጄክቱ በተመረጡ የመንግሥት ጤና ተቋማት የፀሐይ አማራጭን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተለይም የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ባለባቸው የጤና ተቋማት የሚከሰተውን ችግር በማቃለል ረገድ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ተብሏል፡፡

ለመርሐ-ግብሩ ስኬት አጋር ድርጅቶች በዋናነት የዓለም ጤና ድርጅት፣ ጋቪ እና ዩኒሴፍ አሥፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ተገልጿል፡፡

በፈትያ አብደላ እና ሰለሞን ይታየው