Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በጥቅምት ወር ኢትዮጵያ በርካታ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ለማስተናገድ ዝግጅት አድርጋለች – ሰላማዊት ካሳ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በጥቅምት ወር ኢትዮጵያ በርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ኮንፈረንሶችን ለማስተናገድ ዝግጅት ማድረጓን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ካለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ የተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላት በድምቅት መከበራቸውን አስታውሰዋል፡፡

በዓላቱ የሕዝቦችን ትስስር ከማጠናከር ባለፈ የአንድን ሀገር እምቅ ባህል እና እሴት በሚገባ ያንጸባረቁ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በተያዘው ጥቅምት ወር ኢትዮጵያ በርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ኮንፈረንሶችን ለማስተናገድ ዝግጅት ማድረጓን ጠቁመው፤ በዚህ መሰረት ከረሃብ ነጻ የሆነ ዓለም ኮንፈረንስ ከጥቅምት 26 እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ አንስተዋል።

በመድረኩ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ 1 ሺህ 500 እንግዶች እንደሚሳፉ ይጠበቃ ነው ያሉት፡፡

በኮንፈረንሱ ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በምግብ እራስን ለመቻል በተለይም በበጋ ስንዴ፣ በኩታ ገጠም እና በአየር ንብረት ለውጥ ሥራ ያላትን ተሞክሮ የምታካፍል ይሆናል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ስብሰባ ከጥቅምት 9 እስከ 12 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡

ጉባዔው ኢትዮጵያ በቀጣይ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት እቅድ ከመያዟ ጋር ተያይዞ ትልቅ ትርጉም እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡

እንዲሁም 3ኛው የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ በአዲስ አባባ ከጥቅምት 12 ጀምሮ እንደሚካሄድ ጠቁመው÷ ጉባዔው ኢትዮጵያ በሰላምና መረጋጋት በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ሚና እንደምታሳይ ጠቅሰዋል፡፡

የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በሚኖራቸው ቆይታ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እንደሚያደርጉና ተሞክሮ እንደሚለዋወጡም ሚኒስትር ዴዔታዋ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምታስተናግዳቸው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ለቱሪዝም መነቃቃት የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም አመልክተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version