የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ የተጋላጭነት ፈተናዎች ላይ ያተኮረ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

By Melaku Gedif

October 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ የተጋላጭነት ፈተናዎች እና በዓለም አቀፍ ውድድር ውስጥ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

ኮንፍረንሱ “አፍሪካ የተጋላጭነት ፈተናዎች፤ በዓለም አቀፍ ውድድር ካሉ እድሎች ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

በመድረኩ የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪዎች እና ባለሙያዎች የአፍሪካ ተጋላጭነት ፈተናዎች መንስኤ እና መፍትሔዎቻቸው እንዲሁም በዓለም አቀፍ ውድድር ያሉ እድሎችን መጠቀም በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ የመወያያ ጽሑፋቸውን ያቀርባሉ።

ቀጣናዊ ሰላምና ደህንነት፣ አፍሪካ ሙስና እና አምባገነንነትን በመዋጋት እየገጠሟት ያሉ ፈተናዎች፣ የአፍሪካ የተፈጥሮ ሃብቶች አጠቃቀም እና የዓረቡ ዓለም እና የአፍሪካ ትብብርና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይም ጽሑፎች እንደሚቀርቡ የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትም በውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ፣ በሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር በማከናወን ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት የፖሊሲ አማራጭ ምክረ ሃሳቦችን ያቀርባል።

መድረኩን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት እና የአልጀዚራ የጥናቶች ማዕከል በጋራ አዘጋጅተውታል።