Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የዲጂታል ሥርዓቱ ነጻና ሉዓላዊ እንዲሆን የሳይበር ደህንነት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል – አቶ ማሞ ምህረቱ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የዲጂታል ሥርዓቱን ነጻና ሉዓላዊነቱ የተረጋገጠ ለማድረግ ለሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ

ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ወር “የቁልፍ መሠረተ ልማት ደህንነት ለዲጂታል ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው የሳይበር ደህንነት ወር በሳይንስ ሙዚዬም ተጀምሯል።

በመርሐ ግብሩ አቶ ማሞ ምህረቱ እንዳሉት÷ የዲጂታል ሃብቶችን የመጠበቅ እና የዜጎችን ደህንነት በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ ለሳይበር ደህንነት ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

የኢትዮጵያ የዲጂታል ሥርዓት ነጻና ሉዓላዊነቱ የተረጋገጠ እንዲሆንም ለሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመው÷ ለዚህም የባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት።

በሳይበር ቴክኖሎጂ ልማት የግሉ ዘርፍ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት በማገዝ የወጣቶችን የቴክኖሎጂ ተሰጥኦ ማበልጸግ እንደሚገባ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግሥት ሃሚድ በበኩላቸው÷ በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ዕቅድ መሠረት የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሳይበር ደህንነት ወር መከበር የዜጎችን ግንዛቤ ከማሳደግ አንጻር የላቀ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው÷በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን በማክሸፍ ከቢሊየን ብር ኪሣራ መታደግ መቻሉን አስታውሰዋል።

Exit mobile version