የሀገር ውስጥ ዜና

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የዜጎችን የኑሮ ዘይቤ ለመቀየር በትብብር እንደሚሰራ ገለጸ

By Shambel Mihret

October 10, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ በዘላቂነት ለመቀየር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይና ካንትሪ ዳይሬክተር ዝላታን ሚሊስክን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)÷የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለኢትዮጵያ ከሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ በዘላቂነት ለመቀየር የሚሰራውን ሥራ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ተቋሙ በማህበራዊ ጥበቃ፣ በከተማና የገጠር ሴፍቲኔት ፕሮግራምና በኮቪድ -19 ወቅት ላበረከተው አስተዋፅኦ እውቅና ሰጥተዋል።

በተጨማሪም በቀጣይ በማህበራዊ ጥበቃና በሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በተለይም በግብርናው እንዲሁም በአቅም ግንባታ ዘርፎች በትብብር እንዲሰራ ጠይቀዋል።

ዝላታን ሚሊስክን በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በምግብ ራስን ለመቻል እያደረገች ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገመግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

በቀጣይም ፕሮግራሙ ከሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ በዘላቂነት ለመቀየር የሚያደርገውን ጥረት ለመቀጠል ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብርና በቅንጅት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡