Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት ዩናይትድ ኪንግደም ድጋፍ እንድታደርግ ጠየቀች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከዩናይትድ ኪንግደም የንግድና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ዴዔታ ዳግላስ አሌክሳንደር ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ ኢትዮጵያ በቅርቡ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ ያተኮረ ሲሆን÷በዚሁ ወቅት ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ማሻሻያዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሃላፊዎቹ ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብርና ዩናይትድ ኪንግደም ለኢትዮጵያ ልማት እያደረገች ያለውን የልማት ድጋፍ ላይ መክረዋል፡፡

ማሻሻያቹ መልካም ጅማሮ መሆናቸውን በመግለጽ ኢትዮጵያ ባለሃብቶችን መሳብ የሚያስችል አቅም እንዳላት መገለጹንም የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያደረገች ያለውን ጥረት ለማፋጠን ቁርጠኛ መሆኗን ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን ሒደት ላይ የሚሰራው ቡድን ሊቀመንበር የሆነችው ዩናይትድ ኪንግደም አስፈላጊውን ድጋፍ እንድታደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ውይይቱ በለንደን ከተካሄደው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ዓለም አቀፍ ፎረም ጎን ለጎን ነው የተደረገው፡፡

 

Exit mobile version