የሀገር ውስጥ ዜና

ሃን ካንግ በስነ ጽሁፍ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆኑ

By Melaku Gedif

October 10, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ ኮሪያዊቷ ሃን ካንግ በስነ ጽሁፍ ዘርፍ የ2024 የኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆን ችለዋል፡፡

የ53 ዓመቷ ሃን የልብ ወለድ ደራሲ ከዚህ ቀደም በፈረንጆቹ 2007 በጻፉት ‘ዘ ቬጀተሪያን’ በተሰኘው መፅሐፋቸው አማካኝነት የ2016 ማን ቡከር ኢንተርናሽናል የስነ ጽሁፍ ሽልማት አሸናፊ ነበሩ፡፡

በወቅቱ መጽሐፉ ለሽልማት ሊበቃ የቻለው በፈረንጆቹ በ2015 በዲቦራህ ስሚዝ አማካኝነት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጉሞና ታትሞ ለንባብ በመብቃቱ እንደሆነ ተገልጿል።

በስነ ጽሁፍ ዘርፍ ከፈረንጆቹ 1901 ጀምሮ እየሸለመ ያለው የኖቤል ኮሚቴ ሃን ካንግን ጨምሮ 18 ሴቶችን በዘርፉ በአሸናፊነት ሸልሟል።

የኖቤል አሸናፊዋ ሃን 810 ሺህ ፓውንድ የሚበረከትላቸው መሆኑ ተነግሯል፡፡

ሃን የመጀመሪያዋ ደቡብ ኮሪያዊ የኖቤል አሸናፊ መሆናቸውን ኮሚቴው ጠቁሟል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡