Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሀገር ውስጥ የቡና ተጠቃሚነት ትርጉም ባለው መልኩ እድገት አሳይቷል – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር ውስጥ የቡና ተጠቃሚነት ትርጉም ባለው መልኩ እድገት አሳይቷል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ ቡና የኢኮኖሚያችን ዋልታ ነው፤ በቡና ልማት ያሳየነው የእድገት ርምጃም ይህንኑ ያንፀባረቀ ነው ብለዋል።

እጅግ አስደናቂ የሆነውን 1 ሚሊየን ቶን ቡና የማምረት ግብ አሳክተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የሀገር ውስጥ የቡና ተጠቃሚነት ትርጉም ባለው መልኩ እድገት ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡

ከተግዳሮቶቻችን ባሻገር በቡና ልማት ዘርፍ የበለጠ ስኬታማ መሆናችንን ቀጥለናል ሲሉ አስገንዝበው፤ በዘርፉ የተሰማሩ ሁሉ ይህን ቁልፍ ኢንዱስትሪ የበለጠ ለማሳደግ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ባለፉት 6 ዓመታት ለእድገቱ ያለንን ቁርጠኝነት በሚያሳይ ሁኔታ 8 ነጥብ 5 ቢሊየን የቡና ችግኞችን ተክለናል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ለቡና የእሴት ሰንሰለት የተሳለጠ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው÷ እሴት የመጨመር ተግባርም ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫችን ነው ብለዋል።

በቀጣይ በጠንካራ ሥራ እና ፈጠራ ፀንተን ስኬቶቻችንን ማስቀጠልና ማስፋት አለብን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

Exit mobile version