አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ1 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የላኪነት ፈቃድ በማውጣት የቡና ምርታቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ እያቀረቡ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሀገራዊ የቡና ኤግዚቢሽንና የእውቅና መርኃ-ግብር ”ቡናችን ለብልጽግናችን ” በሚል መሪ ሐሳብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት÷የኢትዮጵያ የቡና ልማት በጥራትና ምርታማነቱ አድጎ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱም ከፍተኛ ጭማሬ እያሳየ መምጣቱን ገልፀዋል።
በአምራች አርሶ አደሮች 1 ኪሎ ግራም ባለ ልዩ ጣዕም ቡና ከ100 ሺህ ብር በላይ እየተሸጠ መሆኑን ጠቁመው፤ ከቡና የእሴት ሰንሰለት የሚያገኙት ድርሻም እያደገ መጥቷል ብለዋል።
ከ1 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የላኪነት ፈቃድ በማውጣት የቡና ምርታቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ እያቀረቡ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የጂ-25 ቡና አምራች ሀገራትን በሊቀመንበርነት በመምራት ላይ እንደምትገኝ ጠቁመው፤ የአፍሪካ 2063 ስትራቴጂክ የንግድ ምርት ሆኖ እንዲሰየም ለሕብረቱ ጉባዔ ያቀረበችው ጥያቄም ተቀባይነት ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና የትግበራ ሂደት በቀዳሚነት ወደ ግብይት ከሚገቡ ምርቶች መካከል ቡናን ቀዳሚ የሚያደርገው መሆኑን ሚኒስትሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ(ዶ/ር)በበኩላቸው÷የቡና ልማትን ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር የተጣጣመ በማድረግ ገቢውም እንዲጨምር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም አሁን ላይ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ድርሻ ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 60 በመቶ ማደጉን ገልፀዋል።