አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከ45 የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
የውይይት መድረኩ ፓርቲዎቹ በሀገራዊ ምክክሩ ሊኖራቸው የሚገባውን ሚና እና ተሳትፎ ለማጎልበት ታስቦ የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) ÷ ኮሚሽኑ ካለፈው የውይይት መድረክ ወዲህ ያከናወናቸውን ተግባራት አስረድተው በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራትን ጠቁመዋል፡፡
ከሀገራዊ ምክክር መድረኩ ራሳቸውን ያገለሉ እና በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ ወገኖች ወደ ምክክር መድረኩ እንዲመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ኮሚሽኑ ምክረ-ሀሳቦችን ለመሰብሰብ መነሻ የሚሆኑ ጥያቄዎችን በማቅረብ በግብዓትነት ሊወሰዱ የሚችሉ በርካታ ሀሳቦች እንዲንሸራሸሩ መደረጉን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡