የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ በባህል፣ ታሪክና ሐይማኖት ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ተስማሙ

By Feven Bishaw

October 10, 2024

 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ)ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል ያለውን የባህል፣ የታሪክና የሐይማኖት ግንኙነት ለማጠናከር ተስማሙ፡፡

በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት በሞሮኮ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ልዑክ ከሞሮኮ የኢንዶውመንትና የሐይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር አሕመድ ተውፊቅ ጋር ተወያይቷል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የሞሮኮ ሕዝብ በባህልና ሐይማኖት ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ገልፀው ዕሴቶቹን በሀገራቱ መካከል እያደገ ለመጣው የሁለትዮሽ ግንኙነት መጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡

የሞሮኮ የሐይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር አሕመድ ተውፊቅ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ለነቢዩ መሐመድ በዋለችው ውለታ ሀገሪቱ በመላው ሙስሊሙ ልብ ውስጥ ያለች ሀገር መሆኗን ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል ያለውን የባህል፣ የታሪክና የሐይማኖት ግንኙነት ለማጠናከር ተቋማቸው ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል፡፡