የሀገር ውስጥ ዜና

በሊባኖስ የዜጎች ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

By Melaku Gedif

October 10, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሊባኖስ በተፈጠረው ቀውስ የዜጎች ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው በሰጡት መግለጫ÷ የሊባኖስ ቀውስን ተከትሎ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ለዜጎች ደህንነት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ቀውሱን ተከትሎ በተቋቋመው የቴክኒክና ብሔራዊ ኮሚቴ በሊባኖስ ቆንስላ በተሰራው ስራ እስካሁን 51 ዜጎችን ወደ ሀገር መመለስ መቻሉንና ለችግር ተጋላጭ የሆኑና ወደ ሀገር መመለስ የሚፈልጉ 3 ሺህ ዜጎች መመዝገባቸውም ታውቋል።

ምዝገባው አሁንም በአካል፣ በስልክና በኦንላይን አማራጮች ቢቀጥልም በሚጠበቀው ልክ ዜጎች እየተመዘገቡ እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ ወደ ሀገር መመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን በቀረቡት አማራጮች እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ ባለፈ አንፃራዊ ሰላም ወዳለባቸው የሊባኖስ አካባቢዎች ዜጎች እንዲዘዋወሩ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው ያሉት አምባሳደር ነቢያት፤ ዜጎች ችግር ላይ እንዳይወድቁ የማድረጉን ስራ ለማጠናከርና ለማፋጠን የተለያዩ አመራሮችን ያካተተ ልዑክ ወደ ስፍራው ማቅናቱንም ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ም/ቤት ለ3ኛ ጊዜ አባል ሆና መመረጧንና በ79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ውጤታማ የዲፕሎሲ ተሳትፎ እንደነበራት ተገልጿል።

ከጉባኤው ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ልዑክ የተመድ ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ጨምሮ ከፀጥታው ም/ቤት ቋሚና ተለዋጭ አባል ሀገራት ጋር ውይይት ማድረጉም ተመልክቷል።

በጉባኤው ኢትዮጵያ የራሷንና አህጉራዊ ጥቅሞችን የሚያስጠብቁ አቋሞችን አንፀባርቃለች ተብሏል።

በውብርስት ተሰማ