የሀገር ውስጥ ዜና

የዘር እሴት ሰንሰለትን ለማሻሻል የምርምር ስራ ጉልህ ሚና ይጫወታል- ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

By Melaku Gedif

October 10, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘር እሴት ሰንሰለትን ለማሻሻል የምርምር ስራ ያለው ሚና ወሳኝ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ።

በማሽላ የዘር ስርዓት ላይ ያተኮረ ውይይት በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ ጋቢሳ ኤጀታ (ፕ/ር) እንዲሁም በዘርፉ የተሰማሩ አመራሮች እና ሳይንቲስቶች ተገኝተዋል።

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት የዘር እሴት ሰንሰለት ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠቁመው÷ የምርምር ስራ ለዘርፉ ያለው አበርክቶ ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈቶ ኢስሞ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ዘር ለግብርና ዘርፍ ያለው አስፈላጊነት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የውይይቱ ዓላማ በማሽላ የዘር ሥርዓት ላይ ውይይት በማድረግ ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ መሆኑን ገልጸዋል።

ጋቢሳ ኤጀታ (ፕ/ር)÷ የማዳቀል ዘር ሥርዓት በአሜሪካ ከተጀመረ ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ መሆኑን አንስተው በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ጋር የተናበበ የሰው ኃይል አስፈላጊ እንደሆነ ማስገንዘባቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።