የሀገር ውስጥ ዜና

በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ አካባቢዎች ቀላልና መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ

By amele Demisew

October 10, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት 10 ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የሀገሪቱ ክፍሎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ዝናብ ሰጭ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በደቡብ፣ ምስራቅ፣ ደቡብ ምዕራብና ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ ገጽታ እንደሚኖራቸውም ተገልጿል።

በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት ከኦሮሚያ ክልል ባሌ እና ምስራቅ ባሌ፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ቦረና እና ምስራቅ ቦረና ዞኖች፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ፣ ወላይታ፣ ኮንሶ፣ አማሮ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች፤ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ፣ ኮንታ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች፤ ሁሉም የሲዳማ ክልል ዞኖች፤ ከሶማሌ ክልል ፋፋን፣ ኤረር፣ ጀረር፣ ኖጎብ፣ ሊበን፣ ቆራሂ ዶሎ፣ ዳዋ፣ ሊበን፣ አፍዴር እና ሸበል ዞኖች፤ እንዲሁም ሀረሪ እና ድሬዳዋ ላይ በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ቀላልና መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተጠቁሟል፡፡

የክረምት ወቅት ዝናብ እያገኙ በነበሩት በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ እንዲሁም በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ዝናቡ ቀጣይነት እንደሚኖረው ተመላክቷል።

እንዲሁም በፀኃይ ሀይል ታግዞ ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች ጋር ተያይዞ በምዕራብና ቄለም ወለጋ፣ ኢሉባቦር፣ ቡኖ በደሌ፣ ጅማ፤ ከፋ፣ ሸካና ማጂ አከባቢዎች ላይ በጥቂት ስፍራዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉዱሩ ወለጋ፣ አርሲ እና ምዕራብ አርሲ፤ ምስራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል፣ አሶሳ፣ ካማሺ እና የማኦኮሞ ልዩ ዞን፤ ከጋምቤላ ክልል የኢታንግ ልዩ ዞን፣ ኑዌር፣ አኝዋ እና ማጃንግ ዞኖች በብዙ ቦታዎቻቸው ላይም ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተጠቅሷል፡፡

ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር፣ ምስራቅ፣ ምዕራብ እና ሰሜን ጎጃም፣ የሰሜን፣ የደቡብ እና የማዕከላዊ ጎንደር፣ አዊ ዞኖች እና ባህርዳር ዙሪያ፤ ከትግራይ ክልል የሰሜን ምዕራብ እና የምዕራብ ዞኖች ላይ ቀላል መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ትንበያው ጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ከአማራ ክልል በሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ዋህግምራ፤ ሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞኖች፤ ከትግራይ ክልል የደቡብና የደቡብ ምስራቅና ዞኖች፤ ከአፋር ክልል ፋንቲ፣ ማሂ፣ ሃሪ እና ጋቢ ዞኖች፤ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ፣ ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ሰሜን ሸዋ (ሰላሌ)፤ አዲስ አበባ፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡