የሀገር ውስጥ ዜና

ብሪታኒያ ለኢትዮጵያ የ22 ነጥብ 9 ሚሊየን ፓውንድ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች

By Melaku Gedif

October 10, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪታኒያ መንግስት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ የሚውል የ22 ነጥብ 9 ሚሊየን ፓውንድ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡

የብሪታኒያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስቴር በዛሬው እለት እንዳስታወቀው÷ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚውል የ16 ሚሊየን ፓውንድ ድጋፍ ይደረጋል።

ድጋፉ የቀድሞው ተዋጊዎችን መልሶ በማቋቋም ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የሚውል መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በተመሳሳይ የብሪታኒያ መንግስት በኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍን ለመደገፍ የሚውል እና ለሶስት አመታት የሚቆይ የ6 ነጥብ 9 ሚሊየን ፓውንድ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የብሪታኒያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር አኒልሴ ዶዶስ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎችን ይጎበኛሉ የተባለ ሲሆን፤ በጉብኝታቸውም የብሪታኒያ ድጋፍ ምን ውጤት እንዳመጣ ይመለከታሉ ተብሎ ይጠበቃል።