አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጦላይ የባለሌላ ማዕረግተኛ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሲያሰለጥናቸው የቆዩ መሰረታዊ ወታደሮችን አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የመከላከያ ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጀኔራል አብዱራህማን እስማኤልን ጨምሮ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ተገኝተዋል።
የጦላይ ባለሌላ ማዕረግተኛ ወታደራዊ ስልጠና ትምህርት ቤት አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ጡምሲዶ ፊታሞ ባደረጉት ንግግር ÷ ዘመናዊና የሰለጠነ ሰራዊት ለሀገር ህልውና ከመሆንም ባለፈ የተከበረውን ሙያ ለትውልድ ማሻገር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የጦላይ የባለሌላ ማዕረግተኛ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በየጊዜው የሀገር አለኝታ የሆኑ የሰራዊት አባላትን በማፍራት በስኬት መንገድ ቀጥሎ እስካሁንም የዘለቀ መሆኑን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለትም በትምህርት ቤቱ የፕሮፌረሽናል ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱና ሀገራቸውን በላቀ ብቃት የሚያገለግሉ መሰረታዊ ወታደሮች ለምርቃት መብቃታቸውን ገልጸዋል።
መሰረታዊ ወታደሮቹ በሥነ ልቦና ግንባታ፣ የመከላከያ እሴቶች፣ የውጊያ እና ሌሎች ልዩ ልዩ ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በመሆኑም ወታደሮቹ የሀገር አስተማማኝ መከታ በመሆን የውጭም ይሁን የውስጥ ጠላትን በአስተማማኝ መልኩ የመመከት የላቀ ብቃት እንዳላቸውም አረጋግጠዋል።