አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የተከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች የከፋ ጉዳት እንዳላደረሱ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የመሬት መሰንጠቅ፣ የእሳተ-ገሞራ ፍንዳታ፣ ሱናሚ፣ የመሬት መንሸራተትና ሌሎችም ዓለም የምታስተናግዳቸው የተፈጥሮ አደጋዎች መሆናቸው ያስገነዘበው ኢንስቲትዩቱ÷ የመሬት መንቀጥቀጥ በመሬት ውስጥ አለቶች ግጭት ሲፈጥሩ ወይም ሲላቀቁ በሚፈጠረው ክፍተት ከፍተኛ ድምፅ ሲገባ የሚከሰት ድንገተኛ የተፈጥሮ አደጋ ነው ብሏል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጥና እሱን ተከትሎ የሚከሰት ንዝረት ደግሞ በተለያዩ ዓለማት ከንብረት ውድመት እስከ ህይወት መቅጠፍ የደረሰ አደጋ ማድረሳቸውን በማስታወስ÷ በፈረንጆቹ 1960 በቺሊ የተከሰተውና በሬክተር ስኬል 9 ነጥብ 5 የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ በምድር ላይ የከፋውና ከፍተኛው መሆኑን ገልጿል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኢጃራ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ መገኛ እንደመሆኗ በተለያዩ ጊዜያት የመሬት መንቀጥቀጥ አጋጥሟታል፤ የከፋ ጉዳት ባያደርስም በ1900 ዓ.ም 6 ነጥብ 7፣ በ1909 ዓ.ም 6 ነጥብ 8 እንዲሁም በ1961 ዓ.ም 6 ነጥብ 5 በሬክተር ስኬል የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጥን ጨምሮ የሥነ-ምድር አደጋዎች በእርግማን ወይም ቁጣ የሚከሰቱ ሳይሆን መሬት ተፈጥሯዊ ሥራዋን እየሰራች ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ÷ ኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ መገኛ በመሆኗ የሥነ-ምድር አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ገልጸው፤ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል፡፡
የሥነ-ምድር አደጋ መቼ ሊከሰት እንደሚችል ማወቅ ባይቻልም እንደ ተቋም የተደራጀ መረጃ መስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የጂኦፊዚክስ ምርምር ሥራ አስፈጻሚ ገነት አሰፋ በበኩላቸው÷ የመሬት መንቀጥቀጥ በአለቶች ግጭትና መላቀቅ፣ በእሳተ-ገሞራ፣ በኬሚካልና ኒውክሌር ፍንዳታ እንዲሁም በሰው ሰራሽ መንገድ ሊከሰት እንደሚችል ጠቅሰው÷ በኢትዮጵያ የሚከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች በእሳተ-ገሞራና በአለቶች ግጭት የሚፈጠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ሰሞኑን በፈንታሌ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋም በ10 ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ በ4 ነጥብ 9 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ በመሆኑ የጉዳት መጠኑ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመው÷ አደጋውን ተከትሎ በአዲስ አበባ፣ ደሴ፣ አሰበ ተፈሪና ሌሎችም አካባቢዎች ንዝረት እንደነበር ገልፀዋል።
ሕብረተሰቡ የመሬት መንቀጥቀጥም ሆነ ንዝረት ሲያጋጥም ቅድሚያ በመረጋጋት ለአደጋ ከሚያጋልጡ እንቅስቃሴዎች መታቀብ እንዳለበት ያስገነዘቡት ደግሞ በኢንስቲትዩቱ የጂኦፊዚክስ ከፍተኛ ተመራማሪ ዕዝራ ታደሰ ናቸው፡፡