አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ ከ2025-2027 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሦስተኛ ጊዜ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆና ተመረጠች፡፡
ኢትዮጵያ ለሦስተኛ ዙር የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል በመሆን የተመረጠቸው በ79ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ነው፡፡
ቀደም ሲል በፈረንጆቹ ከ2013 እስከ 2015 እና ከ2016 እስከ 2018 ባለው ጊዜ ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል በመሆን ማገልገሏ ይታወሳል፡፡
አሁን ደግሞ ለሦስትኛ ጊዜ መመረጧ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ውሳኔ ሰጪ ያደርጋታል መባሉን በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በነበራት የአባልነት ጊዜ ለሰብዓዊ መብቶች መጠበቅ እንዲሁም በተለያዩ ሀገራት ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በትጋት መሥራቷ በጉባዔው ተነስቷል፡፡
ለሦስተኛ ጊዜ በመመረጧም ምክር ቤቱ ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጎልበት በሚያደርገው ጥረት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ድጋፍ እንድታደርግ ያግዛል ነው የተባለው፡፡