Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያና ፈረንሳይ ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንዲጠናከር እንሠራለን- አምባሳደር አሌክሲ ለሜክ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኢትዮጵያ አዲስ ከተሾሙት የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲ ለሜክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ ከፈረንሳይ ጋር በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አስረድተዋል፡፡

የፈረንሳይ ኩባንያዎችም በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ግንኙነት አድንቀው÷ ፈረንሳይ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት እንድትደግፍ ጠይቀዋል።

አምባሳደር አሌክሲ ለሜክ በበኩላቸው÷ ፈረንሳይ ኢትዮጵያ እያደረገች ላለችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጠንካራ ድጋፍ እንደምትሰጥ አረጋግጠዋል፡፡

ሁለቱ አገራት በኢኮኖሚ መስክ ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሠሩም ነው ያረጋገጡት፡፡

በተመሳሳይ አምባሳደር ምስጋኑ በኢትዮጵያ አዲስ ከተሾሙት የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኤምስበርገር ጋር የተወያዩ ሲሆን÷ በዚሁ ወቅት ለአምባሳደሯ በቀጣናዊ ወቅታዊ ጉዳዮች እና ኢትዮጵያ እየተገበረችው ስላለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በሽግግር ፍትሕ እና በሀገራዊ የምክክር ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት በሀገር ውስጥ እና በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ በመሆናቸው ሕብረቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

አምባሳደሯም ኢትዮጵያ በቀጣናው የሕብረቱ ቁልፍ አጋር መሆኗን በመግለጽ÷ ይህን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሠሩ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

 

 

Exit mobile version