የሀገር ውስጥ ዜና

የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎችን ልኬት ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ዘመናዊ መሳሪያ ሥራ ላይ እንደሚውል ተጠቆመ

By Mikias Ayele

October 09, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎችን ልኬት ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አዲስ ዘመናዊ መሳሪያ ሥራ ላይ ሊውል መሆኑን የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍቅረአብ ማርቆስ እንደገለፁት÷ የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎች በተለይም ለሕክምና አገልግሎት በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡

በተለይም የራጅ፣ ሲቲ ስካን፣ አልትራሳውንድና ሌሎችም የሕክምና አገልግሎቶችን የሚሰጡ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን አንስተዋል።

ለመሳሪያዎቹ አገልግሎት ውጤታማነትና ጉዳቶችን ለመከላከል የልኬት ትክክለኛነታቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ በዚሁ መሠረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም የጨረራ አመንጪ የሕክምና እና ሌሎች መሳሪያዎችን የልኬት ትክክለኛነት ማረጋገጥ የሚያስችል ማዕከል በአዲስ መልክ በማቋቋም ሥራ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለዚህም በ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ዘመናዊ የመሳሪያ ግዥ መከናወኑን አስታውሰው፤ በቅርቡ ተከላው ተጠናቆ ሥራ ይጀምራል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።