አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፍልሰት ስምምነት አጀንዳዎች በተለያዩ የልማት ፖሊሲዎችና ዕቅዶች ውስጥ ተካተው ተፈጻሚ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ ትገኛለች ሲሉ የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
የዓለም አቀፍ የፍልሰት ስምምነት አህጉራዊ ስብሰባ በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት አስተባባሪነት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው።
በስብሰባው ላይ የተገኙት ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2018 የጸደቀውን ዓለም አቀፍ የፍልሰት ስምምነትን በመተግበር ላይ ትገኛለች።
ከስምምነቱ 20 አጀንዳዎች ውስጥ ለአስሩ ቅድሚያ መስጠቷን ጠቅሰው፤ አጀንዳዎቹ በተለያዩ የልማት ፖሊሲዎችና ዕቅዶች ውስጥ ተካተው ተፈጻሚ እየሆነ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዚህም መደበኛ ያልሆነውን ፍልሰት በመከላከልና በመቆጣጠር እንዲሁም መደበኛ ፍልሰትን በማስፋት ከፍልሰት የሚገኘውን ጥቅም አሟጦ በመጠቀም ረገድ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቧን ገልጸዋል።
በብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት አማካኝነት የስምምነቱን ሀገር አቀፍ የአፈጻጸም ሪፖርት በ2020 ለተመድ ማቅረቧን አስታውሰው፤ በየጊዜው በሚደረጉ የአፈጻጸም ግምገማ መድረኮች ላይም የነቃ ተሳትፎ ስታደርግ ቆይታለች ብለዋል።
ይህ ተግባሯም በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪዋ ሻምፒዮን ሀገር በመሆን የስምምነቱን አተገባበር ውጤታማ በማድረግ ተጠቃሽ እንድትሆን አድርጓቷል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የፍልሰት መነሻ፣ መተላለፊያ ብሎም መዳረሻ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሀገር አቀፍ የትብብር ጥምረት ካውንስል በማቋቋም እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ካውንስሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ መሆኑንም ጠቁመዋል።