አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በትኩረት እየሰራች መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስቴሩ ያዘጋጀውና ከአንድ ወር በኋላ የሚካሄደውን “ኢትዮ_ግሪን ሞቢሊቲ 2024” የተሰኘ ዐውደ ርዕይና ሲምፖዚየምን የተመለከተ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ ዛሬ ማምሻውን ተካሂዷል፡፡
ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።
የትራንስፖርት ዘርፉ ከ10 እስከ 15 በመቶ ለአየር ብክለት መንስኤ መሆኑን ገልጸው፤ በዘላቂ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ የታዳሽ ኃይል የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ወይም ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች የማድረግና ምቹ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ አበክሮ እየሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በዐውደ ርዕዩ ከ700 በላይ የአፍሪካ የዘርፍ ተዋንያን እንደሚሳተፉ ጠቅሰው፣ ይህ ለዐውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች ትልቅ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ሚኒስቴሩ ይህን ወሳኝ ዐውደ ርዕይ ስኬታማ ለማድረግ ገቢ ማሰባሰብ በማስፈለጉ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ እንደተዘጋጀ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡