Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

መንግሥት ከፍ ያለውን ድጎማ የሚያደርግበት ለአንድ ዓመት የሚዘልቅ የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ተግባራዊ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ)መንግሥት ከፍ ያለውን ድጎማ የሚያደርግበት ለአንድ ዓመት የሚዘልቅ የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የነዳጅ ሪፎርም አፈጻጸም የደረሰበትን ደረጃ እና የቀጣይ አቅጣጫ አስመልክቶ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አማካሪ አህመድ ቱሳ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የነዳጅ የሪፎርም ሥራ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ጥሩ የሚባል ውጤት ማምጣቱን አንስተዋል።

የሪፎርሙ ተግባራዊነት በዋናነት መንግሥት ላይ የነበረውን የዕዳ ጫና ያቃለለ፣ ኮንትሮባንድን መቆጣጠር ያስቻለ እና የነዳጅ ግብይትን ፈጣንና ዘመናዊ ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ጥቅል ድጎማ ከ197 ቢሊየን ብር በላይ በመንግሥት ድጎማ መደረጉን የጠቆሙት አማካሪው፤ ለሁሉም የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርቶችም ከጥቅል ድጎማው በተጨማሪ ከ30 ቢሊየን ብር በላይ ድጎማ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ረገድ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ሁኔታ ያገናዘበና ሀገር አቀፍ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ታሳቢ ያደረገ የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

በዚህም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በገበያ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተጽዕኖ ያገናዘበ የዋጋ ማስተካከያ ስትራተጂ ተነድፎ ወደ ሥራ እንዲገባ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

በስትራተጂው መሠረትም መንግሥት ከፍ ያለውን ድጎማ የሚያደርግበት ለአንድ ዓመት የሚዘልቅ የተሟላ የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት በነጭ ናፍጣ ላይ 80 በመቶ ድጎማ እንዲሁም በቤንዚን ላይ 75 በመቶ ድጎማ የሚደረግ ይሆናል፡፡
የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግም መንግሥት በዓመት እስከ 300 ቢሊየን ብር ወጪ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ መንግሥት ለነዳጅ ድጎማ ከ35 ቢሊየን ብር በላይ ድጎማ ማድረጉንም ገልፀዋል።

የብዙኃን ትራንስፖርት ላይ የነበረው ድጎማ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል ሲሆን፤ መንግሥት ወደ ሕብረተሰቡ ሊሄድ የሚችለውን ጫና ለማቃለል ይሰራልም ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የድጎማ ሥርዓቱ የኢኮኖሚውን ወቅታዊ ሁኔታና የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም እንዲሁም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በገበያ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተጽዕኖ ያገናዘበ መሆኑንም አስረድተዋል።

Exit mobile version