የሀገር ውስጥ ዜና

የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

By amele Demisew

October 08, 2024

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በ 4ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ካቢኔው ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈባቸው ዋና ዋና አጀንዳዎች ፡-

1ኛ. የኮሪደር ልማት የግዥ ጥያቄ፣ የግንባታ በጀት እና የግዢ ሂደት አወሳሰን በተመለከተ በፋይናንስ ቢሮ በኩል ለቀረበለት ጥያቄ፤ ለልማቱ መሳለጥ እና የሀብት መባከን እንዳይፈጠር እንዲሁም የሥራ ቅልጥፍናን በሚጨምር መንገድ ለመስራት እንዲያስችል የሚያደርግ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተወያይተን አፅድቀዋል::

2ኛ. በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት የሚተዳደሩ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን አያያዝ ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለማረም እና ወደ ከተማው ደረጃውን የጠበቀ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አስተዳደር ዘይቤ ማምጣት እንዲያስችሉ ተቋማቱ በትምህርት ቢሮ ይዞታ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲገቡ የሚያስችላቸው ደንብ አስፈላጊ በመሆኑ አፅድቋል።

3ኛ. የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሰው ኃይል ስምሪት በማዕከል፣ በክፍለ ከተማ እና በወረዳ ለማመጣጠን እንዲቻል በተዘጋጀው የዝውውር እና ምደባ ረቂቅ ደንብ በየተቋማቱ ያለንን የሰው ሀብት በውጤታማነት ለመጠቀም እንዲያችል የሚያግዝ በመሆኑ በሙሉ ድምፅ ማጽደቃቸውን የከተማው ከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡