አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሂዝቦላህ በሰሜናዊ እስራኤል ወደምትገኘው ሃይፋ ከተማ ከ100 በላይ ሮኬቶችን አስወነጨፈ።
ከተማዋ እንዲህ አይነት ጥቃት ሲያጋጥማት ከ18 ዓመታት በኋላ እንደሆነ ተገልጿል።
እስራኤል በሊባኖስ ውስጥ በአየርና በእግረኛ ጦር አማካኝነት ለምትፈጽመው ጥቃት አጸፋ እየመለሰ ያለው ሂዝቦላህ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል እያስወነጨፈ ስለመሆኑ ቢቢሲ ዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሊባኖስ መዲና የሆነችው ቤይሩት ባለስልጣናት በከተማዋ ከስጋት ነጻ የሆነ ስፍራ የለም ሲሉ ተናግረዋል።
እስራኤል በበኩሏ የሂዝቦላህ ይዞታዎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት እየፈጸመች እንደሆነ ገልጻ፤ በጥቃቷ የተገደሉትን የሂዝቦላህ መሪ ሀሰን ነስላህን በመተካት የቡድኑ ሃላፊ ሊሆን ይችላል የተባለው ግለሰብ ባለፈው ሳምንት ሳይገደል እንዳልቀረ አስታውቃለች።
የእግረኛ ጦሯ በደቡብ ምዕራብ ሊባኖስ በተሰጠው ስምሪት በድንበር አካባቢ ተልዕኮውን እየተወጣ ስለመሆኑም አመልክታለች።