አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በእነ ቀሲስ በላይ መኮንን መዝገብ ላይ በተሰሙ የምስክሮችን ቃል መርምሮ ብይን ለመስጠት ለአራተኛ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በተከሳሾች ቄስ በላይ መኮንን፣ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራው እያሱ እንዳለ ወ/መስቀል፣ በኮሚሽን ስራ ላይ በተሰማራው በረከት ሙላቱ ጃፋር እና አለምገና ሳሙኤል ዲንሳ እና የኒሞና ንግድ ስራ ኃላ/የተ/የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አበራ መርጋ ተስፋዬ በተባሉት ላይ ከባድ ማታለል ሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
በዚህም ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ ቁጥር 32 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና የሙስና ወንጀሎች ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር 2 እና ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ እና በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ ቁጥር 382 ንዑስ ቁጥር 1 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ከአፍሪካ ህብረት ምንም አይነት የክፍያ ትእዛዝ ባልተሰጠበት ሁኔታ ላይ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር ለተከሰሱ ተከሳሾች በተለያዩ የዶላር መጠን ክፍያ ይፈጸምላቸው የሚል አጠቃላይ የ 6 ሚሊየን 50 ሺህ ዶላር ሀሰተኛ የክፍያ ሰነድ በአንደኛ ተከሳሽ መቅረቡ ተጠቅሶ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ከባድ ማታለል ሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቷል።
በዚህ መልኩ የቀረበውን ክስ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ብቻ ችሎት የቀረቡና የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን÷ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች በአድራሻቸው ባለመገኘታቸውና በተደጋጋሚ ቀጠሮ ባለመቅረባቸው ለጊዜው ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል።
ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ክሱ እንዲሻሻልላቸው ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ነጥቦችን ፍርድ ቤቱ መርምሮ ወደፊት በማስረጃ እንደሚጣራ ገልጾ መቃወሚያቸውን አልተቀበለውም።
ከዚህም በኋላ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው ተከሳሾቹ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ህግ የአፍሪካ ህብረት ቅርጫፍ የባንክ ባለሙያዎችን አጠቃላይ ሶስት ምስክሮችን አቅርቦ ምስክርነታቸውን አሰምቶ ነበር፡፡
በዚህም ዐቃቤ ህግ ቀረበ ስለተባለው ሀሰተኛ የክፍያ ሰነድና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የምስክር ጭብጥ በማስመዝገብ በዋና ጥያቄ ምስክሮቹን ቃል ያሰማ ሲሆን÷ በዕለቱ የተከሳሽ ጠበቆች ለምስክሮች በመስቀለኛ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በፍርድ ቤቱ የማጣሪያ ጥያቄ ተነስቶ ከምስክሮች መልስ ተሰጥቶበት እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ህግ ምስክር ቃል መርምሮ ብይን ለመስጠት ከሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሶስት ጊዜ ቀጥሮ ነበር፤ ይሁንና ዛሬም በነበረ ቀጠሮ በተለያዩ ስራዎችና ምክንያት መዝገቡ ተመርምሮ ተሰርቶ አለመጠናቀቁ መዝገቡን በሚመለከቱት ዳኛ በኩል ተገልጾ በድጋሚ ለ4ኛ ጊዜ ለጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀጥሯል።
በታሪክ አዱኛ