አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እና የሐይማኖት ተቋማት በቀጣይ በጋራ በሚሠሯቸው ተግባራት ላይ ግብረ-ኃይል በማቋቋም በትብብር ለመስራት ተስማሙ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሐይማኖት ተቋማትን ሚና እና ተሳትፎ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ለማጎልበት ያለመ ውይይት በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ አባላት እና በጉባዔው በአባልነት ያልተመዘገቡ የሐይማኖት ተቋማት መሳተፋቸውን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) በመድረኩ ላይ እንዳሉት÷ ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሐይማኖት ተቋማት ሚና ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በእጅጉ የጎላ ነበር፡፡
ኮሚሽኑ የተሳታፊዎችን ልየታ ባከናወነበት ወቅት የሐይማኖት ተቋማቱ የኮሚሽኑ ተባባሪ አካል በመሆን ላበረከቱት በጎ አስተዋፅኦም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ተቋማቱ በአጀንዳ ልየታ ሂደት ላይ ተሳትፎ በማድረግ፣ የምክክር ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን በፀሎት በማገዝ እንዲሁም ለየእምነቱ ተከታይ ስለ ሀገራዊ ምክክሩ ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ ያበረከቱትን አስተዋጽኦም አድንቀዋል፡፡
ኮሚሽኑ እስከ አሁን ያከናወናቸው ዐበይት ተግባራት በመድረኩ ቀርበው ሀሳብና አስተያየት የተሰጠበት ሲሆን÷ በቀጣይ በጋራ ሊከናወኑ በሚገባቸው ተግባራት ላይም የጋራ ግብረ-ኃይል በማቋቋም በትብብር ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡